ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከአራት ወራት በፊት የታሰረው ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ከእስር እንዲፈታ የሚጠይቅ ዘመቻ ጀመረ።

“የኢትዮ ኒውስ” ዩትዩብ ዜና ማሰራጫ መሥራቹ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለው ከአራት ወራት በፊት ኅዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም ነበር። ጋዜጠኛዉ በቁጥጥር ስር ከዋለ ወራቶች ቢቆጠሩም፤ እስከዛሬ ፍርድ ቤት አልቀረበም፤ የታሰረበት ምክንያት አልተገለፀም፤ ምርመራም አልተደረገበትም።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ የታሰረው፤ „በአማራ ክልል ያለውን ግጭት አስመልክቶ በሠራው ዘገባ ነው ተብሎ ቢታመንም የታሰረበት ምክንያት አልተገለጸለትም“ብሏል።

ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ

የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል ለተፈጠረው ግጭት “ሌሎች ሰባት ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ አስሮ ጥቂቶችንም ከእስር ፈትቷል” ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ባደረገዉ መግለጫ አስታዉቋል።

“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ያሰሯቸዉን ጋዜጠኛ በላይ ማናዬን እና ሌሎች ሁለት ጋዜጠኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ” አምነስቲ ዘመቻውን አስመልክቶ በድረ ገጹ ይፋ ባደረገዉ መልዕክት አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የተደነገገዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስታከዉ “ፕሬሱን እና ሰላማዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን ተጠቅመውበታል” ሲል አምነስቲ ከሷል።

አምነስቲ ሰዎች በድረ ገጹ የተጋራውን የደብዳቤ ቅጂ ወይም በራሳቸው የጻፉትን ድብዳቤ ተጠቅመው ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ ጠይቋል ሲል ዲ ደብሊው ዘግቧል።

By hareya